የአብክመ ስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ደሴ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ እና በስነ-ምግባር የታነጸ ትውልድ ለመቅረጽ ያለመ ሰፊ የስልጠና መድረክ በደሴ ከተማ ተካሄደ።
የመድረኩን መክፈቻ ንግግር ያደረጉት የደሴ ከተማ ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ፍቅር አበበ እንደገለጹት ትምህርት የወደፊት ሀገራዊ ለውጥና የነገዋ ሀገር ተረካቢ ትውልድ መቅረጫ ዋና መሰረት መሆኑን ጠቁመው፤ እንደ ሀገር ያሉትን ዘርፈ ብዙ ተግዳሮቶች፣ የሌብነት፣ የእድገት ወደኋላ ቀርነትና የሰላም እጦት ችግሮችን ዘላቂ በሆነ መልኩ መፍታት የሚቻለው በትምህርትና የአስተሳሰብ ለውጥ በማምጣት ብቻ መሆኑን አስምረውበታል።
ስልጠናው የተዘጋጀው የደሴ ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን የደሴ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ጋር በመተባበር ነው።
በመድረኩ ላይ ከደሴ ከተማ ትምህርት ቤቶች የተወጣጡ ርዕሳነ መምህራን እና የሥነ-ምግባር ክበብ አስተባባሪ መምህራን የተሳተፉ ሲሆን፣ “ለሀገር ተረካቢ ትውልድ የሥነ-ምግባር ግንባታ የትምህርት መዋቅሩ ሚና” በሚል ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ ጥልቅ ውይይት ተደርጓል።
በአብክመ ስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ደሴ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የስነ-ምግባር ግንባታና ሙስና መከላከል ትምህርትና ስልጠና ባለሙያ አቶ ሀብታሙ አሰፋ “ለሀገር ተረካቢ ትውልድ የሥነ-ምግባር ግንባታ የትምህርት መዋቅሩ ሚና” በሚል ርዕሰ ጉዳይ ላይ ስልጠና ሰጥተዋል።